የኪንታሮት የጤና ችግር፤ መነሻ ምክንያቶቹና ሕክምናው ምንድን ነው?
ቅዱስ ሚካኤል የባህል ህክምና
ሀኪም ሰለሞን አዳሙ


ከስሙ ብንጀምር በአማሪኛ የተሰጠው “ኪንታሮት” የሚል ስም ትክክለኛ ሁኔታውን የሚገልፅ አይደለም፤ ምክንያቱም የጤና ችግሩ የሚከሰተው በፊንጢጣ እና በታችኛው ሽለላአንጀት አካባቢ የሚገኙ የደም ስሮች መላላትና መለጠጥ እንዲሁም በደም በመወጠር ማበጥና መግተርተር ነው፤ ይህ ሁኔታ ሰዎች እግር ላይ ተቆጣጥሮና አብጦ እንደሚታየው ግትርትር ደም መላስ በሽታ ወይም ቫሪኮስ ቬይን ነው፡፡ ስሙ የተለመደ በመሆኑ እንጠቀመው፡፡ ኪንታሮት መነሻ ምክንያቶቹ ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ፤ አብዛኛውን ጊዜ ግን በደም ስሮች ላይ በሚፈጠር ጫና የሚከሰት ነው፡፡ በመሆኑም በወሊድ ወቅት የሚኖረው ምጥ ወይም ዓይነ ምድር ለመጸዳዳት ሲባል የሚደረግ ማማጥ በሆድ፣ በሽለላአንጀት እና በፊንጢጣ አካባቢ ግፊት የሚጨምር በመሆኑ ሊፈጠር ይችላል፡፡ የጠቀስናቸው እንቅስቃሴዎች በፊንጢጣና በትልቁ አንጀት አካባቢ ካሉት ደም መላሽ ቧንቧዎች የሚመለሰውን ደም ሊያግዱ ይችላሉ፡፡ በዚህ መንገድ የፊንጢጣ ኪንታሮት ተብለው የሚጠሩ ግትርትር ደም መላሽ ቧንቧዎች ይፈጠራሉ፤ ከፍተኛ ስቃይም ሊያስከትሉ ይችላሉ። ይህ ሁኔታ በሽለላአንጀት ውስጥ የሚፈጠር ወይም በፊንጢጣ ቆዳ ስር የሚፈጠር ሊሆን ይችላል፤ በመሆኑም በሁለት ተከፍሎ የውስጥና የውጭ ኪንታሮት ይባላል፡፡

የውስጥና የውጭ ኪንታሮት የሚፈጠሩበት መንገድና አካባቢያቸው

የውስጥ ኪንታሮት፡- የሚገኘው በሽለላአንጀት ውስጥ ሲሆን በግልፅ የማይታይና የማይሰማንም ነው፤ በመሆኑም ብዙም ምቾት የመንሳት ነገር ላይኖረው ይችላል፤ ነገር ግን በምንፀዳዳበት ወቅት በሚደርስበት ጫና ጉዳት ስለሚገጥመው ደም መፍሰስና ሕመም ሊከሰት ይችላል፡፡ የውስጥ ኪንታሮት በማማጥ ወቅት በሚደርስበት ጫና ወደፊንጢጣ አሞጥሙጦ ሊወጣ ይችላል፤ ይህ ሁኔታ ሲያጋጥም ከፍተኛ ሕመም ሊያጋጥም ይችላል፡፡

የውጪ ኪንታሮት፡- ይኸኛው ደግሞ የሚፈጠረው በፊንጢጣ ቆዳ ስር ሲሆን ሊያብጥ፣ ሊያሳክክና የደም መፍሰስ ሁኔታ ሊኖረው ይችላል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ በረጋ ደም የሚፈጠር ኪንታሮት ይኖራል፤ ይኸውም በውጪኛ ፊንጢጣ ደም ስሮች ውስጥ ደም በመሰብሰብ ሊረጋ ይችላል፤ ርጉ ደም ይባላል፡፡ ይህ ሁኔታ ሲፈጠር እብጠት፣ ከፍተኛ ሕመም፣ መለብለብና እንደ መጅ ያለ በፊንጢጣ አካባቢ ደድሮ የሚቀር ሊሆን ይችላል፡፡

የኪንታሮት በሽታ የተለያዩ ምልክቶች

የኪንታሮት በሽታ የተለያዩ ምልክቶች የሚያሳይ ሲሆን ከነኝህ ውስጥ

ስንፀዳዳ ምንም ሕመም የሌለው ደም መፍሰስ፣

በፊንጢጣ አካባቢ የማሳከክና የመቆጣት ሁኔታ፣

በምንፀዳዳበት ወቅት ከፍተኛ ሕመም መሰማት፣

ስንቀመጥ ሕመምና ምቾት ማጣት፣

ሰገራ በሚጠረግበት ጊዜ በመጥረጊያው ላይ የደም እንጥፍጣፊ ማየት፣

በንክኪ ወቅት ከፍተኛ ሕመም፣

በሽንት ቤት መቀመጫ ላይ የደም ጠብታዎች ማየት፣

በፊንጢጣ አካባቢ የተቆጣጠሩ እብጠቶች፣

በፊንጢጣ አካባቢ እንደ መጅ ያለ እብጠት ሊሆን ይችላል፡፡

ይህ በሽታ የሚፈጠረው በሽለላአንጀት እና በፊንጢጣ አካባቢ ማለትም በዐይነምድር መውጫ የአንጀት ክፍል የሚገኙ የደም ስሮች ከሚገባው በላይ በመላላትና በመለጠጥ እብጠት መፍጠር ነው፡፡ በደም ስሮች ውስጥ ደም እንደመዘዋወሩ መጠን በተለጠጡ በላሉ ደም ስሮች ውስጥ የሚተላለፍ ደም ግፊት በመፍጠር የደም ስሮቹ የበለጠ በመለጠጥ እንዲወጠሩ ያደርጋል፡፡ በዚህ መንገድ የተፈጠረ እብጠት ለመቀመጥም ሆነ ለመፀዳዳት ችግር በመፍጠር ሕመም ያስከትላል፡፡

የኪንታሮት ጤና ችግር እንዳለብን እንዴት ይታወቃል?

ደም ከሰገራ ጋር ወይም በፊንጢጣ መውጣት ከኪንታሮት በተጨማሪ ከአንጀት የጤና ችግሮች ጋር ተያያዥነት ያለው ምልክት ሊሆን ይችላል፤ በመሆኑም ይህ ዘዴ ብቸኛ ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም፤ ነገር ግን ከሰገራ ጋር የሚታይ ደም የኪንታሮት ሁኔታ መኖሩን ሊያመለክት ይችላል፡፡ ከደም በተጨማሪ ሐኪሞች አኖስኮፒ እና ሲግሞይዶስኮፒ የተባሉ መሳሪያዎችን ተጠቅመው ምርመራዎችን በማድረግ የኪንታሮት ሁኔታ መኖሩን ሊያውቁ ይችላሉ፡፡ አኖስኮፒ ፊንጢጣና አካባቢውን ለማየት የሚያስችል ሲሆን ሲግሞይዶስኮፒ ደግሞ በፊንጢጣ አድርጎ እስከ ትልቁ አንጀት ክፍል ዘልቆ ማየት የሚችል መሳሪያ ነው፡፡ እነኝህ መሳሪያዎች የካሜራ ዐይን ያላቸው በመሆኑ ችግሩ ያለበትን የአካል ክፍል በደንብ የሚያሳዩ ናቸው፡፡

የሚሰጠው ሕክምና ምንድነው?

የኪንታሮት ሕመም አብዛኛውን ጊዜ ከአኗኗር ዘይቤ ጋር የመያያዝ ሁኔታ አለው፤ በመሆኑም ችግሩ ሲያጋጥም በመጀመሪያ መፈተሽ ያለብን እሱን ነው፤ ለምሳሌ የሆድ ድርቀት ሊያመጡ የሚችሉ ምግቦችን የምናዘወትር ከሆነ፣ በአንድ ቦታ ለረዥም ሰዓት ያለእንቅስቃሴ የምንቀመጥ ከሆነ፣ የዕለት ኑሯችን ውጥረት የበዛውና ሌሎች ተመሳሳይ ዝንባሌዎች ካሉን እነርሱን በማስተካከል ልዩነቶችን ማየት አለብን፡፡ ሁኔታው ተከስቶብን ከፀናብን ደግሞ የሕክምና አማራጮችን ልንጠቀም እንችላለን፡፡

የጤና ችግሩ እየተባባሰ ከሄደ ደግሞ እስከ ቀዶ ጥገና የሚደርስ ሕክምና ሊያስፈልግ ይችላል

በሕክምናው የተለያዩ መድኃኒቶች ሊታዘዙና ሊወሰዱ ይችላሉ፤ ሐኪምና የመድኃኒት ባለሙያተኛን በማማከር ሊወሰድዱ ይችላሉ፤ የጤና ችግሩ እየተባባሰ ከሄደ ደግሞ እስከ ቀዶ ጥገና የሚደርስ ሕክምና ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ከቀዶ ጥገና በፊት የሚቋጥረውን እብጠት በሙቀት ኃይል በማኮማተር ለመቆጣጠር የሚያስችል ሕክምና ያለ ሲሆን እንደአማራጭ ሊቀርብ ይችላል፡፡ በቀዶ ጥገና ሁለት ዓይነት ሕክምናዎች ሊሰጡ ይችላሉ፤ አንደኛ ያበጠውን አካል በጎማ ማሰር ሲሆን ሌላኛው ደግሞ አካሉን ቆርጦ ማውጣት ሊሆን ይችላል፡፡

የኪንታሮት በሽታ በብዙዎች ላይ የሚከሰት የጤና ችግር ሲሆን ከአራት ሰዎች ሦሥቱ በህይወት ዘመናቸው ያጋጥማቸዋል ተብሎ ይገመታል፡፡ በተለይ ሕመሙ ለረዥም ሰዓት በሚቀመጡ ሰዎች ላይ ሊበረታ ይችላል፡፡ የኪንታሮት በሽታ መታከም የሚችልና የአኗኗር ዘይቤ ላይ ለውጦችን በማድረግ ልንከላከለው የምንችለው ነው፤ ይህንን የጤና ችግር ለመከላከል ሌሎች የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ ነው፡፡ ከጥንቃቄ ርምጃዎች ውስጥ ከዚህ በታች የተጠቀሱት ዋነኛ የሚባሉ ናቸው፡፡

ከጥጥ የተሰሩ የውስጥ ሱሪዎችን መልበስ፣

ንፅህናን በየዕለቱ መጠበቅ፣

ችግሩ ያለበትን አካባቢ ከማከክ መቆጠብ፣

የሆድ ድርቀት ሲያጋጥም ምጥ ሊያባብስ ስለሚችል፤ በአሰር የበለፀጉና ሰገራን የሚለሰልሱ ምግቦች መመገብ፤ ካልሆነም የሰገራ ማለስለሻ መድኃኒቶችን መጠቀም፣

ልስልስ ያላሉና ሊቧጥጡ የሚችሉ የሰገራ መጥረጊያዎችን አለመጠቀም፣

በፊንጢጣ አካባቢ የሕመምና የቁስለት ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ ሌሎች በሽታዎች ስላሉ ሐኪም ዘንድ በመቅረብ ማረጋገጥ፣

በየዕለቱ በቂ ፈሳሽ መጠጣት አስፈላጊ ነው
መልካም ጤንነት !!
• ለበጠ መረጃ ፡- ወደ ቅዱስ ሚካኤል የባህል ህክምና ጎራ በማለት ሀኪም ሰለሞንን ያማክሩ
• ሀኪም ፡- ሰለሞን አዳሙ
• አድራሻ ፡- ቦሌ ሚካኤል በዋናው በር መግቢያ ደሴ ህንፃ ፊትለፊት
Website: www.hakimsolomon.com
ስልክ፡- 0989020202 ወይም ፡- 0911810736
https://www.facebook.com
telgram- https://t.me/kidusmikaelhikmna
Email: info@hakimsolomon.com , solomon@hakimsolomon.com & support@hakimsolomon.com