ሆድ ሕመም እና ተቅማጥ
Author: admin
Date: 2021-06-03
ሆድ ሕመም እና ተቅማጥ
ቅዱስ ሚካኤል የባህል ህክምና
ሀኪም ሰለሞን አዳሙ
የሆድ ሕመም መንስኤዎች ከብዛታቸው የተነሳ ይኼ ነው ለማለት ይከብዳሉ፡፡ የሆድ ሕመም በብዛት ቀላል ችግሮችን ቢያመላክትም አንዳንዴ ግን ጠንከር ያሉ በሽዎች መገለጫ ነው፡፡
ትክክለኛውን ምክንያት ከሕመሙ ብቻ ተነስቶ ማወቅ ቢከብድም ሌሎች ተጨማሪ የበሽታ ምልክቶች ካሉብሕ እና ከሆድሕ ሕመም ጋር ተያያዥነት ያላቸው ነገሮችን በማየት ከሕመሙ ጀርባ ያለውን ምክንያት ማወቅ ይቻላል፡፡
የሆድ ሕመም አንድ ቦታን ለይቶ አሊያም እንዳለ ሆድሕን አጠቃሎ ሊያም ይችላል፡፡ ከግማሽ በላይ የሆነውን ክፍል የሚያመው አይነት የሆድ ሕመም በቀላል የሕክምና ክትትል ሊድን የሚችል ሲሆን እንደ የምግብ አለመፈጨት( Indigestion)ባሉ በአብዛኛው በሚታዩ ችግሮች ይነሳል፡፡ አንድ ቦታን ብቻ ለይቶ ካመመሕ ደግሞ ከበድ ያለ ችግርን ያመላክታል፡፡ ለምሳሌ እንደትርፍ አንጀት (appendicitis) እና የጨጓራ ቁስል የመሳሰሉ በሽታዎች ዋነኛ ምልክት ነው፡፡ ከዚሕ በተጨማሪ ሆድ ውስጥ የሚገኙ ትልልቅ የአካል ክፍሎች¬ ጉበት እና ጣፊያ በሽታዎችም በዚሕ መልኩ ይገለፃሉ፡፡
የሆድ ቁርጠት (እየመጣ የሚሄድ አይነት ሕመም) ከፈስ እና ሰገራ መጠራቀም ጋር ተያይዞ ይመጣል፡፡ ብዙ ሴቶችም ይኼኛውን አይነት ሕመም የወር አበባቸው በሚታያችው ጊዜ ይኖራቸዋል፡፡ ከተቅማጥ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የሆድ ቁርጠት ምንም እንኳን ሀይለኛ ቢሆንም ብዙ ጊዜ ለክፉ አይሰጥም፡፡ በድንገት የሚነሳ ሃይለኛ ሕመም ደግሞ አንጀት መቀደድን፣ኩላሊት ጠጠርን፣ የሃሞት ከረጢት በሽታዎችን፣ የሴት እንቁላል ማምረቻ (ovaries) ወይም የወንድ የዘር ፍሬ ማማረቻ (testis) መቋጠርን (torsion) አሊያም የትልልቅ የደም ቧንቧ ችግርን ተከትሎ ይመጣል፡፡ እንደዚሕ አይነቱ ሕመም አስቸኳይ ሕክምና ስለሚያስፈልገው በፍጥነት ወደሆስፒታል መሄድ አለብሕ፡፡
በትርፍ አንጀት እና በሃሞት ከረጢት በሽታዎች የሚመጣው ሕመም እንቅስቃሴና ሳል ጋር ይብሳል፡፡አንዳንዴም ከከፍተኛ እንቅስቃሴ በኋላ የሚኖር የጡንቻዎች መኮማተር (ስትራፖ) የዚሕ አይነቱን ሕመም ሊያስከተል ይችላል፡፡
ሆድ ላይ የሚደርስ አደጋን (ግጭት፣ ምት) ተከትሎ ሕመም፣ ማቅለሽለሽ እና ማስታወክ ሊኖር ይችላል፡፡ እነዚሕ የበሽታ ምልክቶች ግን በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ይሻሻላሉ፡፡ ከደቂቃዎች ባለፈ የሚቀጥሉ ከሆነ ሆድ ውስጥ የሚገኙ ጠቃሚ አካላት ጉዳትን ያመላክታል፡፡ ስለዚሕም ወደሆስፒታል መሄድ አለብሕ፡፡
ብዙ መድሃኒቶችም ለሆድ ሕመም አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ እንደድርቀት የመሳሰሉ ያልተፈለጉ ችግሮችን በማምጣት የሆድ ሕመም እንዲከሰት ያደርጋሉ፡፡
የሆድ ሕመምን የሚያመጡ ነገሮች ምንድን ናቸው? ሁሉም ሰው በሕይወቱ ከአንድ ጊዜ በላይ የሆድ ሕመም ያጋጥመዋል፡፡ የሆድ ሕመም በጣም በብዛት የሚታይና ሁሉንም ሰው የሚያጠቃ ችግር ነው። ምንም እንኳን የሆድ ሕመም በየጊዜው የሚከሰት ነገር ቢሆንም ዋናው ነገር ከጀርባው ያለውን ምክንያት አውቆ እራስን መጠበቅ ነው፡፡ ከዛም ባለፈ ሕመሙ መቼ የተደበቀ በሽታን እንደሚያመላክት አውቆ በፍጥነት ወደሆስፒታል መሄድ ተገቢ ነገር ነው፡፡
የሆድ ሕመምን ከሚያመጡ ነገሮች መካከል የሚከተሉት በብዛት የሚታዩት እና ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
የምግብ አለመፈጨት(Indigestion)
የሆድ ድርቀት(Constipation)
ኢንፌክሽን
የወር አበባ
የምግብ አለርጂ
የፈስ እና የሰገራ መጠራቀም
የጨጓራ ቁስል ቡአ (Hernia) ?
Lactose intolerance?
የሃሞት ጠጠር(Gallstones)
የኩላሊት ጠጠር(Kidney stones)
የአሲድ ከጨጓራ ወደ ላይ መመለስGastroesophageal reflux disease (GERD) የትርፍ አንጀት በሽታ (Appendicitis) የምግብ መመረዝ( Food Poisoning) የተለያዩ ሆድ ውስጥ የሚኖሩ ረቂቅ ሕዋሳት ¬
አሜባ፣ ጂያርዲያ
የሆድ ሕመም መቼ ሊያሰጋኝ ይገባል?
በጣም ሀይለኛ የሆድ ሕመም ካለብሕ አሊያም ከሚከተሉት ምልክቶች ጋር የተያያዘ ከሆነ በፍጥነት ዶክተርሕን ማማከር አለብሕ ምክንያቱም ጠንከር ካለ በሽታ ጋር ሊያያዙ ይችላሉ እና፡፡
ትኩሳት ማስታወክ የሆድ ድርቀት ደም ካስታወክሕ ደም የቀላቀለ ሰገራ መተንፈስ ማቃት ሽንት ከመሽናት ጋር የተያየዘ ሕመም እና ቶሎ ቶሎ መሽናት የቆዳ ቢጫ መሆን በእርግዝና ጊዜ የመጣ የሆድ ሕመም ሆድሕ ስትነካውም የሚያምሕ ከሆነ ቀደም ብሎ አደጋ ከደረሰብሕ
ለብዙ ቀናት የቆየ የሆድ ሕመም
የሆድ ሕመም ሕክምና ምንድን ነው? የሆድ ሕመም ሕክምና እንደመንስኤው ይለያያል፡፡ ሚዋጡ መድሃኒቶች ፣ አንቲባዮቲክስ ፣ የአኗኗር ዘዴን ማሻሻል አሊየም ኦፕሬሽን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
የምግብ አለመፈጨት (Indigestion)
የምግብ አለመፈጨት ብዙ ጊዜ ከጨጓራ ቁስለት፣ የሀሞት ከረጢት በሽታዎች ወይም የአሲድ መብዛት ጋር ይያያዛል፡፡ ከምግብ በኋላ ወይም ምግብ በምትበላ ጊዜ በሚኖር የሆድ መነፋት እና ምቾት ማጣት የሚገለፅ ሲሆን አንዳንዴም የማቃጠል እና የሕመም ስሜት አብሮት ይኖራል፡፡
የምግብ አለመፈጨት ምልክቶች ምንድን ናቸው?
የምግብ አለመፈጨት ምክልቶች የሚከተሉትን ያጠቃልላሉ፡፡ እነዚሕ ምልክቶች በጭንቀት እና ስራ በሚበዛበት ግዜ የመጨመር ባሕሪ አላቸው፡፡
የሆድ መነፋት ማግሳት እና የፈስ መብዛት ማቅለሽለሽ እና ማስታወክ የማቃጠል ስሜት የሆድ ሕመም የሆድ መጮሕ የማቃጠል ስሜቱ ጨጓራ ውስጥ የሚገኘው አሲድ ወደላይ ሲመለስ እና ለአሲድ ምቹ ያልሆነ ሽፋን ያለውን የጉሮሮ ክፍልን ሲያቃጥል ይከሰታል፡፡
የምግብ አለመፈጨት ማን ላይ ይከሰታል?
ይሄ ችግር በሁሉም የእድሜ ክልል ያሉ ሴቶችንም ወንዶችንም ያጠቃል፡፡ አልኮል በብዛት መጠጣት፣ ጨጓራን የሚጎዱ እንደ አስፕሪን ያሉ መድሃኒቶችን በብዛት መጠቀም እንዲሁም የጨጓራ ቁስለት እና ጭንቀት ወይም ድብርት( depression) የመሳሰሉ በሽታዎች ያለበት ሰው ለዚሕ ችግር ተጋላጭ ነው፡፡.
የምግብ አለመፈጨት መንስኤዎች ምንድን ናቸው?
የጨጓራ ቁስል፣ የአሲድ ከጨጓራ ወደ ጉሮሮ መምጣት፣ የጨጓራ ካንሰር፣ በስኳር ሕመም የሚመጣ የጨጓራ በሽታ፣ የሆድ ኢንፌክሽኖች፣ የጣፊያ በሽታ የመሳሰሉ በሽታዎች ሊያመጡት ይችላል፡፡ ከመድሃኒቶች ደግሞ እንደ አስፕሪን እና አስፕሪንን የመሳሰሉ የሕመም ማስታገሻ መድሃኒቶች፣ የወሊድ መቆጣጠሪያ ክኒን፣ ለእንቅርት በሽታ የሚወሰዱ መድሃኒቶች፣ አንዳንድ አንቲባዮቲክስ ሊያመጡት ይችላሉ፡፡
ከዚሕ በተጨማሪ የአኗኗር ዘይቤሕም ይወስነዋል፡፡ በፍጥነት መብላት፣ በአንድ ጊዜ ብዙ መብላት፣ብዙ አልኮል መጠጣት፣ ሲጋራ ማጨስ፣ጭንቀት ሊያመጡት ይችላሉ፡፡
በእርግዝና ወቅት መሃል አካባቢ አሊያም ወደመጨረሻ ላይ ሊከሰት ይችላል፡፡ ይኼም ከሆርሞን ለውጥ እና እያደገ ያለው ማሕፀን በምግብ መፍጫ አካላት ላይ ከሚያስከትለው ጫና ጋር ይያያዛል፡፡ አንዳንዴ ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች ጋር የማይያያዝ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ የምግብ አለመፈጨት ያጋጥማል፡፡
የምግብ አለመፈጨት ችግር ሲያጋጥመኝ ምን ላድርግ?
የምግብ አለመፈጨት ምልክቶች እየታዩብሕ ከሆነ ወደሆስፒታል ሄደሕ መታየት አለብሕ፡፡ ምክንያቱም የምግብ አለመፈጨት በብዙ አይነት ምክንያቶች የሚመጣ ከመሆኑ አንፃር ተገቢውን ምርመራ ማድረግን እንመክራለን፡፡ ምንም እንኳን ብዙም አሳሳቢ ምክንያቶች ሊከሰት ቢችልም በዚያው መጠን በጣም የከፉ በሽታዎች መገለጫም ስለሆነ ወደ ዶክተርሀ ሄደሕ መታየት አማራጭ የሌለው ተግባርሕ አድርገው፡፡
ከዚያ ባለፈ ሲጋራ አለማጨስ፣ አልኮል አለማብዛት እንዲሁም የተመጣጠነ ምግብ(በአይነትም በመጠንም) መመገብ ችግርሕን ሊቀርፍልሕ ይችላል፡፡
አሜባ
አሜባ ምንድን ነው?
አሜባ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን የሚያጠቃ በማጉያ መነፅር ብቻ በሚታይና በትናንሽ ረቂቅ ሕዋሳት አማካኝነት የሚመጣ በሽታ ነው፡፡ አሜባ አንጀት ውስጥ የሚኖር ሲሆን ከአንጀት አልፎ እንደጉበት ያሉ አካላትን ያጠቃል፡፡ ዘጠና ከመቶ የሚሆኑ አሜባ ሆዳቸው ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የበሽታውን ምልክት የማያሳዩ ሲሆን በተቀሩት አስር በመቶ ብቻ ተቅማጥ እና ሆድ ቁርጠት የመሳሰሉ ምልክቶች ይታይባቸዋል፡፡
አሜባ እንዴት ሊይዘኝ ይችላል?
በአሜባ የተበከለ ውሃ እና ምግብ ዋና መተላለፊያ መንገዶቹ ናቸው፡፡ ከሰውነት ከወጣ በኋላ ለሳምንታት ምንም ሳይሆን የመቆየት ችሎታ ያለው ሲሆን ያልበሰሉ ምግቦች በተለይም አትክልት መመገብ ለበሽታው ያጋልጣል፡፡
የአሜባ ምልክቶች ምንድን ናቸው?
ምንም እኳን አሜባ ሆድሕ ውስጥ ቢገኝም ምንም ምልክት ላታሳይ አሊያም አልፎ አልፎ ብቻ ሊያስቀምጥሕ ይችላል፡፡ የሆድ ቁርጠት እና ደም የቀላቀለ ተቅማጥ ጠና ባለሕመም ጊዜ ይታያሉ፡፡ ከአንጀት ውጭ ሌላ አካልሕን ካጠቃ ደግሞ ሆድ ቁርጠት፣ ትኩሳት እና በአጠቃላይ ጤናሕ ይጎዳል፡፡ አንዴ አሜባ ከያዘሕ ለአመታት አብሮሕ ሊኖር ይችላል፡፡
የጉበት አሜባ ምንድን ነው?
አንጀት ውስጥ የነበረው አሜባ በደም አማካኝነት ተሰራጭቶ ጉበትን ሊያጠቃ ይችላል፡፡ ጉበት ውስጥ ከገባ በኋላ መግል ይፈጥራል፡፡ በቀኙ የላይኛው የሆድ ክፍል የሚሰማ ሕመም እና ትኩሳት ዋናዎቹ መገለጫዎች ናቸው፡፡ ምንም እንኳን በሽታው ከአንጀት ቢነሳም ተቅማጥ የሚታየው በጣም ጥቂት በሽተኞች ላይ ነው፡፡ ጉበት ውስጥ የተፈጠረው መግል ወደሳምባም ሊዛመት ይችላል፡፡ ከሳምባ እና ጉበት በተጨማሪ ወደልብም ይሄዳል፡፡ ለአሜባ የሚሰጡ መድሃኒቶች የሚያድኑት ሲሆን ተጨማሪ መዘዞችን ካመጣ ወይም ደግሞ በመድሃኒቶቹ ካልዳነ ኦፕሬሽን መሰራት ሊያስፈልግ ይችላል፡፡
አሜባን ምን በማድረግ መከላከል እችላለሁ? ምግብሕን በፅዱ ሁኔታ በማዘጋጀት ይሕንን በሽታ ልትከላከል ትችላለሕ፡፡ አሜባ ከሰውነት ውጭ ብዙ አይነት ሁኔታዎችን ተቋቁሞ የመኖር አቅም ቢኖረውም ሀይለኛ ሙቀትን ስለማይቋቋም የሚጠጣ ውሃን ማፍላት እና ምግቦችን በተለይ አትክልትን በደንብ አብስለሕ መመገብ በበሽታው ከመያዝ ይጠብቅሃል፡፡ ንፁሕ ውሃ መጠጣት በበሽታው የመያዝ እድልሕን በትልቁ ይቀንሰዋል፡፡ ሽንት ቤት ከተጠቀምክ በኋላ እጅሕን መታጠብንም ልማድ አድርገው፡፡
ጃርዲያ
ጂርዲያ ምንድን ነው?
ጂያርዲያ አንጀትን የሚያጠቃ በአይን የማይታይ ረቂቅ ሕዋስ ነው፡፡
ጃርዲያ እንዴት ሊይዘኝ ይችላል? ጃርዲያ ከሰገራ ጋር አብሮ የሚወጣ ሲሆን በዚሕ አይነት ሰገራ የተበከለ ውሃ እና ምግብ መተላለፊያ መንገዶቹ ናቸው፡፡
የጃርዲያ በሽታ ምልክቶቹ ምንድን ናቸው? ጃርዲያ ተቅማጥ፣ ሆድ ቁርጠት፣ ማቅለሽለሽ እና የሆድ መነፋትን ያስከትላል፡፡ እነዚሕን ምልክቶች በተደጋጋሚ ልታይ አሊያም እየመጡ እና እየሄዱ ሊያገጥሙሕ ይችላሉ፡፡ከዚሕ ውጪ ምንም ችግር የማያሰከትል ሲሆን በመድሃኒቶች ይድናል፡፡ ስለዚሕ እነዚሕን ምልክቶች ስታይ ዶክተርሕን አማክረው፡
መልካም ጤንነት !!
• ለበጠ መረጃ ፡- ወደ ቅዱስ ሚካኤል የባህል ህክምና ጎራ በማለት ሀኪም ሰለሞንን ያማክሩ
• ሀኪም ፡- ሰለሞን አዳሙ
• አድራሻ ፡- ቦሌ ሚካኤል በዋናው በር መግቢያ ደሴ ህንፃ ፊትለፊት
Website: www.hakimsolomon.com
ስልክ፡- 0989020202 ወይም ፡- 0911810736
Email: info@hakimsolomon.com , solomon@hakimsolomon.com & support@hakimsolomon.com